፩ሐናንያም የተባለ አንድ ሰው ሰጲራ ከተባለች ከሚስቱ ጋር መሬት ሸጠ፥ ፪ሚስቱም ደግሞ ስታውቅ ከሽያጩ አስቀረና እኩሌታውን አምጥቶ በሐዋርያት እግር አጠገብ አኖረው። ፫ጴጥሮስም። ሐናንያ ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለ ምን ሞላ? ፬ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህን ነገር ስለ ምን በልብህ አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው። ፭ሐናንያም ይህን ቃል ሰምቶ ወደቀ ሞተም፤ በሰሙትም ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ። ፮ጐበዞችም ተነሥተው ከፈኑት አውጥተውም ቀበሩት። ፯ከሦስት ሰዓት ያህል በኋላም ሚስቱ የሆነውን ሳታውቅ ገባች። ፰ጴጥሮስም መልሶ። እስቲ ንገሪኝ፥ መሬታችሁን ይህን ለሚያህል ሸጣችሁትን? አላት። እርስዋም። አዎን፥ ይህን ለሚያህል ነው አለች። ፱ጴጥሮስም። የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ ስለ ምን ተስማማችሁ? እነሆ፥ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር በደጅ ነው አንቺንም ያወጡሻል አላት። ፲ያን ጊዜም በእግሩ አጠገብ ወደቀች ሞተችም፤ ጐበዞችም ሲገቡ ሞታ አገኙአት አውጥተውም በባልዋ አጠገብ ቀበሩአት። ፲፩በቤተ ክርስቲያን ሁሉና ይህንም በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ። ፲፪በሐዋርያትም እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ይደረግ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ነበሩ። ፲፫ከሌሎችም አንድ ስንኳ ሊተባበራቸው የሚደፍር አልነበረም፥ ፲፬ሕዝቡ ግን ያከብሩአቸው ነበር፤ የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ። ፲፭ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር። ፲፮ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካለችው ከተማ ድውያንንና በርኵሳን መናፍስት የተሣቀዩትን እያመጡ ብዙ ሰዎች ይሰበስቡ ነበር፤ ሁሉም ይፈወሱ ነበር። ፲፯ሊቀ ካህናቱ ግን የሰዱቃውያን ወገን ሆነውም ከእርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ተነሡ ቅንዓትም ሞላባቸው። ፲፰በሐዋርያትም ላይ እጃቸውን ጭነው በሕዝቡ ወኅኒ ውስጥ አኖሩአቸው። ፲፱የጌታ መልአክ ግን በሌሊት የወኅኒውን ደጅ ከፍቶ አወጣቸውና። ፳ሂዱና ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ በመቅደስ ንገሩ አላቸው። ፳፩በሰሙም ጊዜ ማልደው ወደ መቅደስ ገብተው አስተማሩ። ግን ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው ሸንጎውንና የእስራኤልን ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድነት ጠሩ፥ ያመጡአቸውም ዘንድ ወደ ወኅኒ ላኩ። ፳፪-፳፬የመቅደስ አዛዥና የካህናት አለቆችም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ። እንጃ ይህ ምን ይሆን? እያሉ ስለ እነርሱ አመነቱ። ፳፭አንድ ሰውም መጥቶ። እነሆ፥ በወኅኒ ያኖራችኋቸው ሰዎች እየቆሙ ሕዝቡንም እያስተማሩ በመቅደስ ናቸው ብሎ አወራላቸው። ፳፮በዚያን ጊዜ አዛዡ ከሎሌዎች ጋር ሄዶ አመጣቸው፥ በኃይል ግን አይደለም፤ ሕዝቡ እንዳይወግሩአቸው ይፈሩ ነበርና። ፳፯አምጥተውም በሸንጎ አቆሙአቸው። ፳፰ሊቀ ካህናቱም። በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ ብሎ ጠየቃቸው። ፳፱ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው አሉ። ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል። ፴እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን የአባቶቻችን አምላክ አስነሣው፤ ፴፩ይህን እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ንስሐን የኃጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ፥ ራስም መድኃኒትም አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው። ፴፪እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፥ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው። ፴፫እነርሱም ሲሰሙ በጣም ተቈጡ ሊገድሉአቸውም አሰቡ። ፴፬ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የሕግ መምህር ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ በሸንጎ ተነሥቶ ሐዋርያትን ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ፥ ፴፭እንዲህም አላቸው። የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ፴፮ከዚህ ወራት አስቀድሞ ቴዎዳስ። እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ ተነሥቶ ነበርና፥ አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎችም ከእርሱ ጋር ተባበሩ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ እንደ ምናምንም ሆኑ። ፴፯ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላው ይሁዳ ተነሣ ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ፤ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ። ፴፰አሁንም እላችኋለሁ። ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና፤ ፴፱ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፥ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ። ፵ሰሙትም፥ ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፥ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው። ፵፩እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ፵፪ዕለት ዕለትም በመቅደስና በቤታቸው ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።