፩በዚያን ቀንም በኢየሩሳሌም ባለች ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ፤ ሁሉም ከሐዋርያትም በቀር ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ አገሮች ተበተኑ። ፪በጸሎትም የተጉ ሰዎች እስጢፋኖስን ቀበሩት ታላቅ ልቅሶም አለቀሱለት። ፫ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ ነበር፤ ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጐተተ ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥ ነበር። ፬የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ። ፭ፊልጶስም ወደ ሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው። ፮ሕዝቡም የፊልጶስን ቃል በሰሙ ጊዜ ያደርጋት የነበረውንም ምልክት ባዩ ጊዜ፥ የተናገረውን በአንድ ልብ አደመጡ። ፯ርኵሳን መናፍስት በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ይወጡ ነበርና፤ ብዙም ሽባዎችና አንካሶች ተፈወሱ፤ ፰በዚያችም ከተማ ታላቅ ደስታ ሆነ። ፱ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ግን። እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ፥ እየጠነቈለ የሰማርያንም ወገን እያስገረመ ቀድሞ በከተማ ነበረ። ፲ከታናናሾችም ጀምሮ እስከ ታላላቆቹ ድረስ። ታላቁ የእግዚአብሔር ኃይል ይህ ነው እያሉ ሁሉ ያደምጡት ነበር። ፲፩ከብዙ ዘመንም ጀምሮ በጥንቈላ ስላስገረማቸው ያደምጡት ነበር። ፲፪ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር መንግሥትና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እየሰበከላቸው ፊልጶስን ባመኑት ጊዜ፥ ወንዶችም ሴቶችም ተጠመቁ። ፲፫ሲሞንም ደግሞ ራሱ አመነ፤ ተጠምቆም ከፊልጶስ ጋር ይተባበር ነበር፤ የሚደረገውንም ምልክትና ታላቅ ተአምራት ባየ ጊዜ ተገረመ። ፲፬በኢየሩሳሌምም የነበሩት ሐዋርያት የሰማርያ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል እንደተቀበሉ ሰምተው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሰደዱላቸው። ፲፭እነርሱም በወረዱ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ጸለዩላቸው፤ ፲፮በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና። ፲፯በዚያን ጊዜ እጃቸውን ጫኑባቸው መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ። ፲፰ሲሞንም በሐዋርያት እጅ መጫን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥ ባየ ጊዜ፥ ገንዘብ አመጣላቸውና። ፲፱እጄን የምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ስጡኝ አለ። ፳ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው። የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ፳፩ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም። ፳፪እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንሰሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤ ፳፫በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና። ፳፬ሲሞንም መልሶ። ካላችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ አላቸው። ፳፭እነርሱም ከመሰከሩና የጌታን ቃል ከተናገሩ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በሳምራውያን በብዙ መንደሮችም ወንጌልን ሰበኩ። ፳፮የጌታም መልአክ ፊልጶስን። ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ አለው። ፳፯ተነሥቶም ሄደ። እነሆም፥ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ ፳፰ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። ፳፱መንፈስም ፊልጶስን። ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው። ፴ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና። በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን? አለው። ፴፩እርሱም። የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው። ፴፪ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። ፴፫በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል? ፴፬ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ። እባክህ፥ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ? አለው። ፴፭ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት። ፴፮በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም። እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው። ፴፯ፊልጶስም። በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ። ፴፰ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም። ፴፱ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፥ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና። ፵ፊልጶስ ግን በአዛጦን ተገኘ፥ ወደ ቂሣርያም እስኪመጣ ድረስ እየዞረ በከተማዎች ሁሉ ወንጌልን ይሰብክ ነበር።