በዚያም ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ መከራ ያጸናባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ በአንዳንዶቹ ላይ እጁን ጫነባቸው። የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው። አይሁድንም ደስ እንዳሰኛቸው አይቶ ጨምሮ ጴጥሮስን ደግሞ ያዘው። የቂጣ በዓልም ወራት ነበረ። በያዘውም ጊዜ ወደ ወኅኒ አገባው ከፋሲካም በኋላ ወደ ሕዝብ ያወጣው ዘንድ አስቦ እያንዳንዱ አራት ወታደሮች ሆነው እንዲጠብቁት ለአራት ጭፍራ ክፍል አሳልፎ ሰጠው። ጴጥሮስም በወኅኒ ይጠበቅ ነበር፤ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አጥብቆ ይደረግ ነበር። ሄሮድስም ሊያወጣው ባሰበ ጊዜ፥ በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ በሁለት ሰንሰለት ታስሮ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ሆነው ወኅኒውን ይጠብቁ ነበር። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና። ፈጥነህ ተነሣ አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ። መልአኩም። ታጠቅና ጫማህን አግባ አለው፥ እንዲሁም አደረገ። ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ አለው። ወጥቶም ተከተለው፤ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ሆነ አላወቀም። የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም አውቆ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ። ፲፩ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ። ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ። ፲፪ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ። ፲፫ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሉአት አንዲት ገረድ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤ ፲፬የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሣ ደጁን አልከፈተችም፥ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች። ፲፭እነርሱም። አብደሻል አሉአት። እርስዋ ግን እንዲሁ እንደ ሆነ ታስረግጥ ነበር። እነርሱም። መልአኩ ነው አሉ። ፲፮ጴጥሮስ ግን ማንኳኳቱን አዘወተረ፤ ከፍተውም አዩትና ተገረሙ። ፲፯ግን ዝም እንዲሉ በእጁ ጠቅሶ ጌታ ከወኅኒ እንዴት እንዳወጣው ተረከላቸውና። ይህን ለያዕቆብና ለወንድሞች ንገሩ አላቸው። ወጥቶም ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ። ፲፰በነጋም ጊዜ። ጴጥሮስን ምን አግኝቶት ይሆን? ብለው በጭፍሮች ዘንድ ብዙ ሁከት ሆነ። ፲፱ሄሮድስም አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ጠባቂዎችን መረመረ ይገድሉአቸውም ዘንድ አዘዘ፤ ከይሁዳም ወደ ቂሣርያ ወርዶ በዚያ ተቀመጠ። ከጢሮስና ከሲዶና ሰዎችም ጋር ተጣልቶ ነበር፤ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ መጡ፥ የንጉሥንም ቢትወደድ ብላስጦስን እሺ አሰኝተው ዕርቅ ለመኑ፥ አገራቸው ከንጉሥ አገር ምግብ ያገኝ ነበረና። ፳፩በተቀጠረ ቀንም ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋን ተቀመጠ እነርሱንም ተናገራቸው፤ ፳፪ሕዝቡም። የእግዚአብሔር ድምፅ ነው የሰውም አይደለም ብለው ጮኹ። ፳፫ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው በትልም ተበልቶ ሞተ። ፳፬የእግዚአብሔር ቃል ግን ያድግና ይበዛ ነበር። ፳፭በርናባስና ሳውልም አገልግሎታቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስንም ከእነርሱ ጋር ይዘውት መጡ።