፩አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና። እንደ ሙሴ ሥርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር። ፪በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ጊዜ፥ ስለዚህ ክርክር ጳውሎና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ሽማግሌዎችም ወደ ኢየሩሳሌም ይወጡ ዘንድ ተቈረጠ። ፫ቤተ ክርስቲያኑም በመንገድ እየረዳቸው እነርሱ የአሕዛብን መመለስ እየተረኩ በፊንቄና በሰማርያ አለፉ፥ ወንድሞችንም ሁሉ እጅግ ደስ አሰኙአቸው። ፬ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት ሽማግሌዎችም ተቀበሉአቸው፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ አወሩ። ፭ከፈሪሳውያን ወገን ግን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነሥተው። ትገርዙአቸው ዘንድና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ታዙአቸው ዘንድ ይገባል አሉ። ፮ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ስለዚህ ነገር ለመማከር ተሰበሰቡ። ፯ከብዙ ክርክርም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው ወንድሞች ሆይ፥ አሕዛብ ከአፌ የወንጌልን ቃል ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደ መረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ። ፰ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው፤ ፱ልባቸውንም በእምነት ሲያነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል አንዳች አልለየም። ፲እንግዲህ አባቶቻችንና እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን እግዚአብሔርን አሁን ስለ ምን ትፈታተናላችሁ? ፲፩ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ እነርሱ ደግሞ እንድን ዘንድ እናምናለን። ፲፪ሕዝቡም ሁሉ ዝም አሉ፥ በርናባስና ጳውሎስም እግዚአብሔር በእጃቸው በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ምልክትና ድንቅ ሁሉ ሲተርኩላቸው ይሰሙ ነበር። ፲፫እነርሱም ዝም ካሉ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ መለሰ። ወንድሞች ሆይ፥ ስሙኝ። ፲፬እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን ተርኮአል። ፲፭ከዚህም ጋር የነቢያት ቃል ይሰማማል፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ። ፲፮-፲፰ከጥንት ጀምሮ ሥራው ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው። ፲፱ስለዚህ ከአሕዛብ ወደ እግዚአብሔር የዞሩትን እንዳናስቸግራቸው፥ ፳ነገር ግን ከጣዖት ርኵሰትና ከዝሙት ከታነቀም ከደምም ይርቁ ዘንድ እንድንጽፍላቸው እቈርጣለሁ። ፳፩ሙሴስ ከቀደሙት ትውልድ ጀምሮ በሰንበት በሰንበት በምኵራቦቹ ሲያነቡ በየከተማው እርሱን የሚሰብኩ አሉት። ፳፪ያን ጊዜ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከቤተ ክርስቲያኑ ሁሉ ጋር ከእነርሱ የተመረጡትን ሰዎች ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ይልኩ ዘንድ ፈቀዱ፤ እነርሱም በወንድሞች መካከል ዋናዎች ሆነው በርስያን የተባለው ይሁዳና ሲላስ ነበሩ። ፳፫እንዲህም ጽፈው በእነርሱ እጅ ላኩ። ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ወንድሞችም በአንጾኪያና በሶርያ በኪልቅያም ለሚኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርባሉ። ፳፬ያላዘዝናቸው ሰዎች ከእኛ ወጥተው። ትገረዙ ዘንድና ሕግን ትጠብቁ ዘንድ ይገባችኋል ብለው ልባችሁን እያወኩ በቃል እንዳናወጡአችሁ ስለ ሰማን፥ ፳፭-፳፯ራሳቸውም ደግሞ በቃላቸው ያንኑ ይነግሩአችሁ ዘንድ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል። ፳፰-፴እነርሱም ተሰናብተው ወደ አንጾኪያ ወረዱ፥ ሕዝቡንም ሰብስበው ደብዳቤውን ሰጡአቸው። ፴፩ባነበቡትም ጊዜ ከምክሩ የተነሣ ደስ አላቸው። ፴፪ይሁዳና ሲላስም ደግሞ ነቢያት ነበሩና ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጸኑአቸው። ፴፫አያሌ ቀንም ከተቀመጡ በኋላ ከወንድሞች በሰላም ተሰናብተው ወደ ሐዋርያት ሄዱ። ፴፬ሲላስ ግን በዚያ ይኖር ዘንድ ፈቀደ። ፴፭ጳውሎስና በርናባስም ከሌሎች ከብዙ ሰዎች ጋር ደግሞ የጌታን ቃል እያስተማሩና ወንጌልን እየሰበኩ በአንጾኪያ ይቀመጡ ነበር። ፴፮ከጥቂት ቀንም በኋላ ጳውሎስ በርናባስን። ተመልሰን የጌታን ቃል በተናገርንበት በየከተማው ሁሉ ወንድሞችን እንጐብኛቸው፥ እንዴት እንዳሉም እንወቅ አለው። ፴፯በርናባስም ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ደግሞ ከእነርሱ ጋር ይወስድ ዘንድ አሰበ፤ ፴፰ጳውሎስ ግን ይህን ከእነርሱ ጋር ሊወስድ አልፈቀደም፥ ከእነርሱ ዘንድ ከጵንፍልያ ተለይቶ ነበርና፥ ወደ ሥራም ከእነርሱ ጋር አልመጣም ነበርና። ፴፱ስለዚህም እርስ በርሳቸው እስኪለያዩ ድረስ መከፋፋት ሆነ፥ በርናባስም ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ። ፵ጳውሎስ ግን ሲላስን መረጠ፥ ወንድሞችም ለእግዚአብሔር ጸጋ አደራ ከሰጡት በኋላ ወጣ፤ ፵፩አብያተ ክርስትያናትንም እያጸና በሶርያና በኪልቅያ ይዞር ነበር።