አጵሎስም በቆሮንቶስ ሳለ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፥ አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ። ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን? አላቸው። እነርሱም። አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት። እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ? አላቸው። እነርሱም። በዮሐንስ ጥምቀት አሉት። ጳውሎስም። ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ አላቸው። ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤ ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው በልሳኖችም ተናገሩ፥ ትንቢትም ተናገሩ። ሰዎቹም ሁሉ አሥራ ሁለት ያህሉ ነበር። ወደ ምኵራብም ገብቶ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያስረዳቸው ሦስት ወር ያህል በግልጥ ይናገር ነበር። አንዳንዶች ግን እልከኞች ሆነው በሕዝብ ፊት መንገዱን እየሰደቡ ባላመኑ ጊዜ፥ ከእነርሱ ርቆ ደቀ መዛሙርትን ለየ፥ ጢራኖስም በሚሉት በትምህርት ቤት ዕለት ዕለት ይነጋገር ነበር። በእስያም የኖሩት ሁሉ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም የጌታን ቃል እስኪሰሙ ድረስ ሁለት ዓመት ያህል እንዲህ ሆነ። ፲፩እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ፲፪ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። ፲፫አጋንንትንም እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶች። ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን እያሉ ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ የጌታን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ዘንድ ሞከሩ። ፲፬የካህናትም አለቃ ለሆነ አስቄዋ ለሚሉት ለአንድ አይሁዳዊ ይህን ያደረጉ ሰባት ልጆች ነበሩት። ፲፭ክፉው መንፈስ ግን መልሶ። ኢየሱስንስ አውቀዋለሁ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ? አላቸው። ፲፮ክፉው መንፈስም ያለበት ሰው ዘለለባቸው ቆስለውም ከዚያ ቤት ዕራቁታቸውን እስኪሸሹ ድረስ በረታባቸው አሸነፋቸውም። ፲፯ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት ሁሉ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ዘንድ የታወቀ ሆነ፥ በሁላቸውም ላይ ፍርሃት ወደቀባቸው፥ የጌታም የኢየሱስ ስም ተከበረ፤ ፲፰አምነውም ከነበሩት እጅግ ሰዎች ያደረጉትን እየተናዘዙና እየተናገሩ ይመጡ ነበር። ፲፱ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ። እንዲህም የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር። ፳፩ይህም በተፈጸመ ጊዜ ጳውሎስ። ወደዚያ ደርሼ ሮሜን ደግሞ አይ ዘንድ ይገባኛል ብሎ በመቄዶንያና በአካይያ አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ በመንፈስ አሰበ። ፳፪ከሚያገለግሉትም ሁለቱን ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን ወደ መቄዶንያ ልኮ ራሱ በእስያ ጥቂት ቀን ቆየ። ፳፫በዚያም ጊዜ ስለዚህ መንገድ ብዙ ሁከት ሆነ። ፳፬ብር ሠሪ የሆነ ድሜጥሮስ የሚሉት አንድ ሰው የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች በብር እየሠራ ለአንጥረኞች እጅግ ትርፍ ያገኝ ነበርና፤ ፳፭እነዚህንም ይህንም የሚመስለውን ሥራ የሠሩትን ሰብስቦ እንዲህ አላቸው። ሰዎች ሆይ፥ ትርፋችን በዚህ ሥራ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ። ፳፮ይህም ጳውሎስ። በእጅ የተሠሩቱ አማልክት አይደሉም ብሎ፥ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብን እንደ አስረዳና እንደ አሳተ አይታችኋል ሰምታችሁማል። ፳፯ሥራችንም እንዲናቅ ብቻ አይደለም፥ እስያ ሁሉ ዓለሙም የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤምስ መቅደስ ምናምን ሆኖ እንዲቆጠር እንጂ፥ ታላቅነትዋም ደግሞ እንዳይሻር ያስፈራል። ፳፰ይህንም በሰሙ ጊዜ ቍጣ ሞላባቸው። የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉም ጮኹ። ፳፱ከተማውም በሙሉው ተደባለቀ፥ የመቄዶንያም ሰዎች የጳውሎስን ጓደኞች ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ከእነርሱ ጋር ነጥቀው በአንድ ልብ ሆነው ወደ ጨዋታ ስፍራ ሮጡ። ጳውሎስም ወደ ሕዝቡ ይገባ ዘንድ በፈቀደ ጊዜ ደቀ መዛሙርት ከለከሉት። ፴፩ከእስያም አለቆች ወዳጆቹ የሆኑት አንዳንዶች ደግሞ ወደ እርሱ ልከው ወደ ጨዋታ ስፍራ ራሱን እንዳይሰጥ ለመኑት። ፴፪ወዲያና ወዲህም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በጉባኤው ድብልቅልቅ ሆኖ የሚበልጡት ስንኳ ስለ ምን እንደተሰበሰቡ አላወቁም ነበርና። ፴፫አይሁድም ሲያቀርቡት፥ እስክንድሮስን ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ገፉት፤ እስክንድሮስም በእጁ ጠቅሶ በሕዝብ ፊት እንዲምዋገትላቸው ወደደ። ፴፬አይሁዳዊ ግን እንደ ሆነ ባወቁ ጊዜ፥ ሁሉ በአንድ ድምፅ። የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ። ፴፭የከተማይቱም ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ። የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፥ የኤፌሶን ከተማ ለታላቂቱ አርጤምስ ከሰማይም ለወረደው ጣዖትዋ የመቅደስ ጠባቂ መሆንዋን የማያውቅ ሰው ማን ነው? ፴፮ይህንም የሚክደው ከሌለ፥ ጸጥ እንድትሉና አንዳች በችኮላ እንዳታደርጉ ይገባል። ፴፯የመቅደስን ዕቃ ያልሰረቁ አምላካችንንም ያልሰደቡ እነዚህን ሰዎች አምጥታችኋቸዋልና። ፴፰ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች ግን በሰው ላይ ነገር እንዳላቸው፥ የመጋቢያ ቀንና አገረ ገዢዎች አሉ፤ እርስ በርሳቸው ይምዋገቱ። ፴፱ስለ ሌላ ነገር እንደ ሆነ ግን አንዳች ብትፈልጉ፥ በተደነገገው ጉባኤ ይፈታል። ዛሬ ስለ ተደረገው። ሁከት ነው ሲሉ እንዳይከሱን ያስፈራልና፤ ስለዚህም ስብሰባ ምላሽ መስጠት አንችልም፥ ምክንያት የለምና። ፵፩ይህንም ብሎ ጉባኤውን ፈታው።