፩እናንተ ወንድሞች አባቶችም፥ አሁን ለእናንተ ነገሬን ስገልጥ ስሙኝ። ፪በዕብራይስጥም ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ ከፊት ይልቅ ዝም አሉ። እርሱም አለ። ፫እኔ የኪልቅያ በምትሆን በጠርሴስ የተወለድሁ፥ በዚችም ከተማ በገማልያል እግር አጠገብ ያደግሁ፥ የአባቶችንም ሕግ ጠንቅቄ የተማርሁ፥ ዛሬውንም እናንተ ሁሉ እንድትሆኑ ለእግዚአብሔር ቀናተኛ የሆንሁ አይሁዳዊ ሰው ነኝ ፬ወንዶችንም ሴቶችንም እያሰርሁ ወደ ወኅኒም አሳልፌ እየሰጠሁ ይህን መንገድ እስከ ሞት ድረስ አሳደድሁ። ፭እንዲህም ሊቀ ካህናቱ ደግሞ ሽማግሌዎቹም ሁሉ ይመሰክሩልኛል፤ ከእነርሱ ደግሞ መልእክትን ለወንድሞቻቸው ተቀብዬ፥ በደማስቆ ያሉትን ደግሞ ታስረው እንዲቀጡ ወደ ኢየሩሳሌም ላመጣ ወደዚያ እሄድ ነበር። ፮ስሄድም ወደ ደማስቆ በቀረብሁ ጊዜ፥ ቀትር ሲሆን ድንገት ከሰማይ ታላቅ ብርሃን በዙሪያዬ አንጸባረቀ፤ ፯በምድርም ላይ ወድቄ። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። ፰እኔም መልሼ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ? አልሁ። እርሱም። አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ አለኝ። ፱ከእኔ ጋር የነበሩትም ብርሃኑን አይተው ፈሩ፥ የሚናገረኝን የእርሱን ድምፅ ግን አልሰሙም። ፲ጌታ ሆይ፥ ምን ላድርግ? አልሁት። ጌታም። ተነሥተህ ወደ ደማስቆ ሂድና ታደርገው ዘንድ ስለ ታዘዘው ሁሉን በዚያ ይነግሩሃል አለኝ። ፲፩ከዚያ ብርሃንም ክብር የተነሣ ማየት ባይሆንልኝ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች እጄን ይዘው እየመሩኝ ወደ ደማስቆ ደረስሁ። ፲፪በዚያም የኖሩት አይሁድ ሁሉ የመሰከሩለት እንደ ሕጉም በጸሎት የተጋ ሐናንያ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ። ፲፫እርሱም ወደ እኔ መጥቶ በአጠገቤም ቆሞ። ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ እይ አለኝ። እኔም ያን ጊዜውን ወደ እርሱ አየሁ። ፲፬እርሱም አለኝ። የአባቶቻችን አምላክ ፈቃዱን ታውቅ ዘንድና ጻድቁን ታይ ዘንድ ከአፉም ድምፅን ትሰማ ዘንድ አስቀድሞ መርጦሃል ፲፭ባየኸውና በሰማኸው በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆንለታለህና። ፲፮አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ። ፲፯ወደ ኢየሩሳሌምም ከተመለሱ በኋላ በመቅደስ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝ፥ ፲፰እርሱም። ፍጠን ከኢየሩሳሌምም ቶሎ ውጣ፥ ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና ሲለኝ አየሁት። ፲፱እኔም። ጌታ ሆይ፥ በአንተ የሚያምኑትን በምኵራብ ሁሉ እኔ በወኅኒ አገባና እደበድብ እንደ ነበርሁ እነርሱ ያውቃሉ፤ ፳የሰማዕትህንም የእስጢፋኖስን ደም ባፈሰሱ ጊዜ፥ ራሴ ደግሞ በአጠገባቸው ስቆም ተስማምቼ የገዳዮችን ልብስ እጠብቅ ነበር አልሁ። ፳፩እርሱም። ሂድ፥ እኔ ወደ አሕዛብ ከዚህ ወደ ሩቅ እልክሃለሁና አለኝ። ፳፪እስከዚህም ቃል ድረስ ይሰሙት ነበር፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው። እንደዚህ ያለውን ሰው ከምድር አስወግደው፥ በሕይወት ይኖር ዘንድ አይገባውምና አሉ። ፳፫ሲጮኹና ልብሳቸውን ሲወረውሩ ትቢያንም ወደ ላይ ሲበትኑ፥ ፳፬የሻለቃው ወደ ሰፈሩ እንዲያገቡት አዘዘ፥ እንደዚህም የጮኹበትን ምክንያት ያውቅ ዘንድ። እየገረፋችሁ መርምሩት አላቸው። ፳፭በጠፍርም በገተሩት ጊዜ ጳውሎስ በአጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ። የሮሜን ሰው ያለ ፍርድ ትገርፉ ዘንድ ተፈቅዶላችኋልን? አለው። ፳፮የመቶ አለቃውም በሰማ ጊዜ ወደ ሻለቃው ቀርቦ። ይህ ሰው ሮማዊ ነውና ታደርገው ዘንድ ካለህ ተጠበቅ ብሎ ነገረው። ፳፯የሻለቃውም ቀርቦ። አንተ ሮማዊ ነህን? ንገረኝ አለው፤ እርሱም። አዎን አለ። ፳፰የሻለቃውም መልሶ። እኔ ይህን ዜግነት በብዙ ገንዘብ አገኘሁት አለ። ጳውሎስም። እኔ ግን በእርስዋ ተወለድሁ አለ። ፳፱ስለዚህም ሊመረምሩት ያሰቡት ከእርሱ ወዲያው ተለዩ፤ የሻለቃውም ደግሞ ሮማዊ መሆኑን ባወቀ ጊዜ ፈራ፥ አሳስሮት ነበርና። ፴በማግሥቱም አይሁድ የከሰሱት በምን ምክንያት እንደ ሆነ እርግጡን ያውቅ ዘንድ አስቦ ፈታው፥ የካህናት አለቆችና ሸንጎውም ሁሉ ይሰበሰቡ ዘንድ አዘዘ፥ ጳውሎስንም አውርዶ በፊታቸው አቆመው።