ጳውሎስም ሸንጎውን ትኵር ብሎ ተመልክቶ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ እስከዚች ቀን ድረስ በመልካም ሕሊና ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኖሬአለሁ አለ። ሊቀ ካህናቱም ሐናንያ አፉን ይመቱት ዘንድ በአጠገቡ ቆመው የነበሩትን አዘዘ። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ። አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ፥ እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው፤ አንተ በሕግ ልትፈርድብኝ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ሕግ እመታ ዘንድ ታዛለህን? አለው። በአጠገቡ የቆሙትም። የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን? አሉት። ጳውሎስም። ወንድሞች ሆይ፥ ሊቀ ካህናት መሆኑን ባላውቅ ነው፤ በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ ቃል አትናገር ተብሎ ተጽፎአልና አላቸው። ጳውሎስ ግን እኵሌቶቹ ሰዱቃውያን እኵሌቶቹም ፈሪሳውያን መሆናቸውን አይቶ። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ፈሪሳዊ የፈሪሳዊም ልጅ ነኝ፤ ስለ ተስፋና ስለ ሙታን መነሣት ይፈርዱብኛል ብሎ በሸንጎው ጮኸ። ይህንም ባለ ጊዜ በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ጥል ሆነ ሸንጎውም ተለያየ። ሰዱቃውያን። ትንሣኤም መልአክም መንፈስም የለም የሚሉ ናቸውና፤ ፈሪሳውያን ግን ሁለቱን ያምናሉ። ታላቅ ጩኸትም ሆነ፥ ከፈሪሳውያንም ወገን የሆኑት ጻፎች ተነሥተው። በዚህ ሰው ላይ ምንም ክፉ ነገር አላገኘንበትም፤ መንፈስ ወይስ መልአክ ተናግሮት ይሆን? ብለው ተከራከሩ። ብዙ ጥልም በሆነ ጊዜ የሻለቃው ጳውሎስን እንዳይገነጣጥሉት ፈርቶ ጭፍሮቹ ወርደው ከመካከላቸው እንዲነጥቁት ወደ ሰፈሩም እንዲያገቡት አዘዘ። ፲፩በሁለተኛውም ሌሊት ጌታ በአጠገቡ ቆሞ። ጳውሎስ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም ስለ እኔ እንደ መሰከርህ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሃልና አይዞህ አለው። ፲፪በጠባም ጊዜ አይሁድ ጳውሎስን እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ በመሐላ ተስማሙ። ፲፫ይህንም ሴራ ያደረጉት ሰዎች ከአርባ ይበዙ ነበር፤ ፲፬እነርሱም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ሽማግሌዎቹ መጥተው። ጳውሎስን እስክንገድል ድረስ ምንም እንዳንቀምስ ተረጋግመን ተማምለናል። ፲፭እንግዲህ አሁን እናንተ ከሸንጎው ጋር ሆናችሁ ስለ እርሱ አጥብቃችሁ እንደምትመረምሩ መስላችሁ ወደ እናንተ እንዲያወርደው ለሻለቃው አመልክቱት፤ እኛም ሳይቀርብ እንድንገድለው የተዘጋጀን ነን አሉአቸው። ፲፮የጳውሎስ የእኅቱ ልጅ ግን ደባቸውን በሰማ ጊዜ፥ መጥቶ ወደ ሰፈሩ ገባና ለጳውሎስ ነገረው። ፲፯ጳውሎስም ከመቶ አለቆች አንዱን ጠርቶ። ይህን ብላቴና ወደ ሻለቃው ውሰድ፥ የሚያወራለት ነገር አለውና አለው። ፲፰እርሱም ይዞት ወደ ሻለቃው ወሰደውና። ይህ ብላቴና የሚነግርህ ነገር ስላለው እስረኛው ጳውሎስ ጠርቶ ወደ አንተ እንድወስደው ለመነኝ አለው። ፲፱የሻለቃውም እጁን ይዞ ፈቀቅ አለና ለብቻው ሆኖ። የምታወራልኝ ነገር ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም። አይሁድ ስለ ጳውሎስ ከፊት ይልቅ አጥብቀህ እንደምትመረምር መስለህ፥ ነገ ወደ ሸንጎ ታወርደው ዘንድ ሊለምኑህ ተስማምተዋል። ፳፩እንግዲህ አንተ በጅ አትበላቸው፤ እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ ተማምለው ከእነርሱ ከአርባ የሚበዙ ሰዎች ያደቡበታልና፤ አሁንም የተዘጋጁ ናቸው የአንተንም ምላሽ ይጠብቃሉ አለው። ፳፪የሻለቃውም። ይህን ነገር ለእኔ ማመልከትህን ለማንም እንዳትገልጥ ብሎ ካዘዘ በኋላ ብላቴናውን አሰናበተው። ፳፫ከመቶ አለቆቹም ሁለት ጠርቶ። ወደ ቂሣርያ ይሄዱ ዘንድ ሁለት መቶ ወታደሮችንና ሰባ ፈረሰኞችን ሁለት መቶም ባለ ጦር መሣሪያዎችን ከሌሊቱ በሦስተኛው ሰዓት አዘጋጁ አላቸው። ፳፬ጳውሎስንም ወደ አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ በደኅና እንዲያደርሱት የሚያስቀምጡበትን ከብት ያዘጋጁ ዘንድ አዘዛቸው። ፳፭ደብዳቤም ጻፈ እንዲህ የሚል። ፳፮ከቀላውዴዎስ ሉስዮስ ወደ ክቡር አገረ ገዡ ወደ ፊልክስ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን። ፳፯ይህን ሰው አይሁድ ይዘው ሊገድሉት ባሰቡ ጊዜ ከጭፍሮቹ ጋር ደርሼ አዳንሁት፥ ሮማዊ እንደ ሆነ አውቄ ነበርና። ፳፰የሚከሰስበትንም ምክንያት አውቅ ዘንድ አስቤ ወደ ሸንጎአቸው አወረድሁት፤ ፳፱በሕጋቸውም ስለ መከራከር እንደ ከሰሱት አገኘሁ እንጂ ለሞት ወይም ለእስራት የሚያደርስ ክስ አይደለም። በዚህም ሰው አይሁድ ሴራ እንዲያደርጉበት ባመለከቱኝ ጊዜ ያን ጊዜውን ወደ አንተ ሰደድሁት፥ ከሳሾቹንም ደግሞ በፊትህ ይከሱት ዘንድ አዘዝኋቸው። ደኅና ሁን። ፴፩ወታደሮቹም እንደ ታዘዙት ጳውሎስን ይዘው በሌሊት ወደ አንቲጳጥሪስ አደረሱት፤ ፴፪በነገውም ከእርሱ ጋር ይሄዱ ዘንድ ፈረሰኞችን ትተው ወደ ሰፈር ተመለሱ። ፴፫እነዚያም ወደ ቂሣርያ ገብተው ደብዳቤውን ለአገረ ገዡ በሰጡ ጊዜ ጳውሎስን ደግሞ በፊቱ አቆሙት። ፴፬ካነበበውም በኋላ የወዴት አውራጃ እንደ ሆነ ጠየቀው፤ የኪልቅያ ሰው መሆኑንም ባወቀ ጊዜ። ፴፭ከሳሾችህ ደግሞ ሲመጡ እሰማሃለሁ አለው፤ በሄሮድስም ግቢ ውስጥ ይጠብቁት ዘንድ አዘዘ።