፩ፊስጦስም ወደ አውራጃው ገብቶ ከሦስት ቀን በኋላ ከቂሣርያ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። ፪የካህናቱ አለቆችና የአይሁድም ታላላቆች በጳውሎስ ላይ አመለከቱ፥ ፫ጳውሎስንም ሲቃወም እንዲያደላላቸው እየለመኑ፥ በመንገድ ሸምቀው ይገድሉት ዘንድ አስበው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያስመጣው ማለዱት። ፬ፊስጦስ ግን ጳውሎስ በቂሳርያ እንዲጠበቅ እርሱም ራሱ ወደዚያ ፈጥኖ ይሄድ ዘንድ እንዳለው መለሰላቸው፤ ፭እንግዲህ በዚህ ሰው ክፋት ቢሆን ከእናንተ ዘንድ ያሉት ባለ ስልጣኖች ከእኔ ጋር ወርደው ይክሰሱት አላቸው። ፮በእነርሱም ዘንድ ከስምንት ወይም ከአስር የማይበልጥ ቀን ተቀምጦ ወደ ቂሳርያ ወረደ፤ በነገውም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ጳውሎስን ያመጡት ዘንድ አዘዘ። ፯በቀረበም ጊዜ ከኢየሩሳሌም የወረዱት አይሁድ ከበውት ቆሙ፥ ይረቱበትም ዘንድ የማይችሉትን ብዙና ከባድ ክስ አነሱበት፤ ፰ጳውሎስም ሲምዋገት። የአይሁድን ህግ ቢሆን መቅደስንም ቢሆን ቄሳርንም ቢሆን አንዳች ስንኳ አልበደልሁም አለ። ፱ፊስጦስ ግን አይሁድን ደስ ያሰኝ ዘንድ ወዶ ጳውሎስን። ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ነገር ከዚያው በፊቴ ትፋረድ ዘንድ ትወዳለህን? ብሎ መለሰለት። ፲ጳውሎስ ግን። እፋረድበት ዘንድ በሚገባኝ በቄሳር ፍርድ ወንበር ፊት ቆሜአለሁ። አንተው ደግሞ ፈጽመህ እንደምታውቅ አይሁድን ምንም አልበደልሁም። ፲፩እንግዲህ በድዬ ወይም ሞት የሚገባውን ነገር አድርጌ እንደ ሆነ ከሞት ልዳን አልልም፤ እነዚህ የሚከሱኝ ክስ ከንቱ እንደሆነ ግን ለእነርሱ አሳልፎ ይሰጠኝ ዘንድ ማንም አይችልም፤ ወደ ቄሳር ይግባኝ ብዬአለሁ አለ። ፲፪በዚያን ጊዜ ፊስጦስ ከአማካሪዎቹ ጋር ተማክሮ። ወደ ቄሳር ይግባኝ ብለሃል፤ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ ብሎ መለሰለት። ፲፫ከጥቂት ቀንም በኋላ ንጉሡ አግሪጳ በርኒቄም ለፊስጦስ ሰላምታ እንዲያቀርቡ ወደ ቂሳርያ ወረዱ። ፲፬በዚያውም ብዙ ቀን ስለተቀመጡ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ እንዲህ ብሎ ገለጠ። ፊልክስ አስሮ የተወው አንድ ሰው በዚህ አለ፤ ፲፭በኢየሩሳሌምም ሳለሁ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች እፈርድበት ዘንድ እየለመኑ ስለ እርሱ አመለከቱኝ። ፲፮እኔም። ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ለፊት ሳይቆም ለተከሰሰበትም መልስ ይሰጥ ዘንድ ፈንታ ሳያገኝ፥ ማንንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሥርዓት አይደለም ብዬ መለስሁላቸው። ፲፯ስለዚህም በዚህ በተሰበሰቡ ጊዜ፥ ሳልዘገይ በማግሥቱ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ ያንን ሰው ያመጡት ዘንድ አዘዝሁ። ፲፰ከሳሾቹም በቆሙ ጊዜ እኔ ያሰብሁትን ክፉ ነገር ክስ ምንም አላመጡበትም፤ ፲፱ነገር ግን ስለ ገዛ ሃይማኖታቸውና ጳውሎስ። ሕያው ነው ስለሚለው ስለ ሞተው ኢየሱስ ስለ ተባለው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ነበር። ፳እኔም ይህን ነገር እንዴት እንድመረምር አመንትቼ። ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ በዚህ ነገር ከዚያ ልትፋረድ ትወዳለህን? አልሁት። ፳፩ጳውሎስ ግን አውግስጦስ ቄሣር እስኪቈርጥ ድረስ እንዲጠበቅ ይግባኝ ባለ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር እስክሰደው ድረስ ይጠበቅ ዘንድ አዘዝሁ። ፳፪አግሪጳም ፊስጦስን። ያንንስ ሰው እኔ ዳግም እኮ እሰማው ዘንድ እወድ ነበር አለው። እርሱም። ነገ ትሰማዋለህ አለው። ፳፫በነገውም አግሪጳና በርኒቄ በብዙ ግርማ መጥተው ከሻለቆችና ከከተማው ታላላቆች ጋር ወደ ፍርድ ቤት ገቡ፤ ፊስጦስም ባዘዘ ጊዜ ጳውሎስን አመጡት። ፳፬ፊስጦስም አለ። አግሪጳ ንጉሥ ሆይ እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ሰዎች ሁሉ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው እየጮኹ የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ በኢየሩሳሌም በዚህም ስለ እርሱ የለመኑኝን ይህን ሰው ታዩታላችሁ። ፳፭እኔ ግን ሞት የሚገባውን ነገር እንዳላደረገ አስተዋልሁ፥ እርሱም ወደ አውግስጦስ ይግባኝ ስላለ እሰደው ዘንድ ቈረጥሁ። ፳፮ስለ እርሱም ወደ ጌታዬ የምጽፈው እርግጥ ነገር የለኝም፤ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን ነገር አገኝ ዘንድ በፊታችሁ ይልቁንም በፊትህ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ አመጣሁት፤ ፳፯እስረኛ ሲላክ የተከሰሰበትን ምክንያት ደግሞ አለማመልከት ሞኝነት መስሎኛልና።