፩-፫በነቢዩ በኢሳይያስ። የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ የተባለለት ይህ ነውና። ፬ራሱም ዮሐንስ የግመል ጠጉር ልብስ ነበረው፥ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሀ ማር ነበረ። ፭ያን ጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤ ፮ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። ፯ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? ፰እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ ፱በልባችሁም። አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና። ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል። ፲አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። ፲፩እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤ ፲፪መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል። ፲፫ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። ፲፬ዮሐንስ ግን። እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር። ፲፭ኢየሱስም መልሶ። አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው። ያን ጊዜ ፈቀደለት። ፲፮ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ ፲፯እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።