በዚያን ጊዜ ጻፎችና ፈሪሳውያን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢየሱስ ቀረቡና። ደቀ መዛሙርትህ ስለ ምን የሽማግሎችን ወግ ይተላለፋሉ? እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው። እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ? እግዚአብሔር። አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ። አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና፤ እናንተ ግን። አባቱን ወይም እናቱን። ከእኔ የምትጠቀምበት መባ ነው የሚል ሁሉ፥ አባቱን ወይም እናቱን አያከብርም ትላላችሁ፤ ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ። እናንተ ግብዞች፥ ኢሳይያስ ስለ እናንተ። ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ። ሕዝቡንም ጠርቶ። ስሙ አስተውሉም፤ ፲፩ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፥ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው አላቸው። ፲፪በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው። ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ አወቅህን? አሉት። ፲፫እርሱ ግን መልሶ። የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። ፲፬ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ አለ። ፲፭ጴጥሮስም መልሶ። ምሳሌውን ተርጕምልን አለው። ፲፮ኢየሱስም እንዲህ አለ። እናንተ ደግሞ እስካሁን የማታስተውሉ ናችሁን? ፲፯ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን? ፲፰ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው። ፲፱ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና። ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ፥ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም። ፳፩ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። ፳፪እነሆም፥ ከነናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል ብላ ጮኸች። ፳፫እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት እያሉ ለመኑት። ፳፬እርሱም መልሶ። ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ። ፳፭እርስዋ ግን መጥታ። ጌታ ሆይ፥ እርዳኝ እያለች ሰገደችለት። ፳፮እርሱ ግን መልሶ። የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ። ፳፯እርስዋም። አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች። ፳፰በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ። አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። ፳፱ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፥ ወደ ተራራም ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችንም፥ ዲዳዎችንም፥ ጉንድሾችንም፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ፥ በኢየሱስም እግር አጠገብ ጣሉአቸው፤ ፈወሳቸውም፤ ፴፩ስለዚህም ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ጉንድሾችም ሲድኑ፥ አንካሶችም ሲሄዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ። ፴፪ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ። ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም አላቸው። ፴፫ደቀ መዛሙርቱም። ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ ይህን ያህል እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን? አሉት። ፴፬ኢየሱስም። ስንት እንጀራ አላችሁ? አላቸው። እነርሱም። ሰባት፥ ጥቂትም ትንሽ ዓሣ አሉት። ፴፭ሕዝቡም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ ፴፮ሰባቱንም እንጀራ ዓሣውንም ይዞ አመሰገነ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። ፴፯ሁሉም በሉና ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሡ። ፴፰የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ። ፴፱ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ መጌዶል አገር መጣ።