ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ፥ እንዲህም አላቸው። በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም አንዳች ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል። ፬-፮ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፥ አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት፥ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ፥ ተቀመጠባቸውም። ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር። ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ። ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ። ፲፩ሕዝቡም። ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው አሉ። ፲፪ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና። ፲፫ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው። ፲፬በመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ ቀረቡና ፈወሳቸው። ፲፭ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው። ፲፮እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት። ኢየሱስም። እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው። ፲፯ትቶአቸውም ከከተማ ወደ ቢታንያ ወጣ በዚያም አደረ። ፲፰በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ። ፲፱በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና። ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው። በለሲቱ ያንጊዜውን እንዴት ደረቀች? ብለው ተደነቁ። ፳፩ኢየሱስም መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፥ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል፤ ፳፪አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው። ፳፫ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና። በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት። ፳፬ኢየሱስም መልሶ። እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤ ፳፭የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው? አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ከሰማይ ብንል። እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ፳፮ከሰው ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን አሉ። ፳፯ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት። እርሱም ደግሞ። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው። ፳፰ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ። ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው። ፳፱እርሱም መልሶ። አልወድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ። ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ። እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም። ፴፩ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው? ፊተኛው አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል። ፴፪ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፥ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም። ፴፫ሌላ ምሳሌ ስሙ። የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። ፴፬የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ። ፴፭ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት። ፴፮ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፥ እንዲሁም አደረጉባቸው። ፴፯በኋላ ግን። ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው። ፴፰ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው። ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ። ፴፱ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል? ፵፩እነርሱም። ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል አሉት። ፵፪ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? ፵፫ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች። ፵፬በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል። ፵፭የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤ ፵፮ሊይዙትም ሲፈልጉት ሳሉ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስላዩት ፈሩአቸው።