፩ኢየሱስም ይህን ነገር ከፈጸመ በኋላ፥ ከገሊላ ሄዶ ወደ ይሁዳ አውራጃ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ መጣ። ፪ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፥ በዚያም ፈወሳቸው። ፫ፈሪሳውያንም ወደ እርሱ ቀረቡና ሲፈትኑት። ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? አሉት። ፬እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ። ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ ፭አለም። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? ፮ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። ፯እነርሱም። እንኪያስ ሙሴ የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት ስለ ምን አዘዘ? አሉት። ፰እርሱም። ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ፤ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም። ፱እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል አላቸው። ፲ደቀ መዛሙርቱም። የባልና የሚስት ሥርዓት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም አሉት። ፲፩እርሱ ግን። ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፤ ፲፪በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፥ ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ፥ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ። ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው አላቸው። ፲፫በዚያን ጊዜ እጁን እንዲጭንባቸውና እንዲጸልይ ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ገሠጹአቸው። ፲፬ነገር ግን ኢየሱስ። ሕፃናትን ተዉአቸው፥ ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉ ናትና አለ፤ ፲፭እጁንም ጫነባቸውና ከዚያ ሄደ። ፲፮እነሆም፥ አንድ ሰው ቀርቦ። መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ? አለው። ፲፯እርሱም። ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ አለው። ፲፰እርሱም። የትኞችን? አለው። ኢየሱስም። አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ ፲፱አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው። ፳ጐበዙም። ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፥ ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው? አለው። ፳፩ኢየሱስም። ፍጹም ልትሆን ብትወድ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው። ፳፪ጐበዙም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ ሄደ። ፳፫ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ። እውነት እላችኋለሁ፥ ለባለጠጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ነው። ፳፬ዳግመኛም እላችኋለሁ፥ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል አለ። ፳፭ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው እጅግ ተገረሙና። እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል? አሉ። ፳፮ኢየሱስም እነርሱን ተመልክቶ። ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል አላቸው። ፳፯በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ። እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን? አለው። ፳፰ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ። ፳፱ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል። ፴ነገር ግን ብዙዎቹ ፊተኞች ኋለኞች፥ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።