ከተራራም በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት። እነሆም፥ ለምጻም ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ እያለ ሰገደለት። እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወዳለሁ፥ ንጻ አለው። ወዲያውም ለምጹ ነጻ። ኢየሱስም። ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ አለው። ወደ ቅፍርናሆምም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሣቀየ በቤት ተኝቶአል ብሎ ለመነው። ኢየሱስም። እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ አለው። የመቶ አለቃውም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በቤቴ ጣራ ከታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ደግሞ ለሌሎች ተገዥ ነኝና፥ ከእኔም በታች ጭፍራ አለኝ፤ አንዱንም። ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም። ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም። ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል አለው። ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ለተከተሉት እንዲህ አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም። ፲፩እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤ ፲፪የመንግሥት ልጆች ግን በውጭ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ፲፫ኢየሱስም ለመቶ አለቃ። ሂድና እንዳመንህ ይሁንልህ አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ። ፲፬ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን በንዳድ ታማ ተኝታ አያት፤ ፲፭እጅዋንም ዳሰሰ፥ ንዳዱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለቻቸው። ፲፮-፲፰ኢየሱስም ብዙ ሰዎች ሲከቡት አይቶ ወደ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዘ። ፲፱አንድ ጻፊም ቀርቦ። መምህር ሆይ፥ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው። ኢየሱስም። ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው። ፳፩ከደቀ መዛሙርቱም ሌላው። ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ እንድሄድ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ አለው። ፳፪ኢየሱስም። ተከተለኝ፥ ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው። ፳፫ወደ ታንኳም ሲገባ ደቀ መዛሙርቱ ተከተሉት። ፳፬እነሆም፥ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ በባሕር ታላቅ መናወጥ ሆነ፤ እርሱ ግን ተኝቶ ነበር። ፳፭ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን እያሉ አስነሡት። ፳፮እርሱም። እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ? አላቸው፤ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፥ ታላቅ ጸጥታም ሆነ። ፳፯ሰዎቹም። ነፋሳትና ባሕርስ ስንኳ የሚታዘዙለት፥ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? እያሉ ተደነቁ። ፳፰ወደ ማዶም ወደ ጌርጋሴኖን አገር በመጣ ጊዜ፥ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ወጥተው ተገናኙት፤ እነርሱም ሰው በዚያ መንገድ ማለፍ እስኪሳነው ድረስ እጅግ ክፉዎች ነበሩ። ፳፱እነሆም። ኢየሱስ ሆይ፥ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን? እያሉ ጮኹ። ከእነርሱም ርቆ የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማራ ነበር። ፴፩አጋንንቱም። ታወጣንስ እንደሆንህ፥ ወደ እሪያው መንጋ ስደደን ብለው ለመኑት። ሂዱ አላቸው። ፴፪እነርሱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ሄዱና ገቡ፤ እነሆም፥ የእሪያዎቹ መንጋ ሁሉ ከአፋፉ ወደ ባሕር እየተጣደፉ ሮጡ በውኃም ውስጥ ሞቱ። ፴፫እረኞችም ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ሄደው ነገሩን ሁሉ አጋንንትም በአደሩባቸው የሆነውን አወሩ። ፴፬እነሆም፥ ከተማው ሁሉ ኢየሱስን ሊገናኝ ወጣ፥ ባዩትም ጊዜ ከአገራቸው እንዲሄድላቸው ለመኑት።