፩ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። ፪በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። ፫እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ፬ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ። ፭እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ፮ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር። ፯ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና። ተነሡ አትፍሩም አላቸው። ፰ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም። ፱ከተራራውም በወረዱ ጊዜ ኢየሱስ። የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው። ፲ደቀ መዛሙርቱም። እንግዲህ ጻፎች። ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል ስለ ምን ይላሉ? ብለው ጠየቁት። ፲፩ኢየሱስም መልሶ። ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናል፤ ፲፪ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ከዚህ በፊት መጣ፤ የወደዱትንም ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም፤ እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ከእነርሱ መከራ ይቀበል ዘንድ አለው አላቸው። ፲፫በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ስለ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው አስተዋሉ። ፲፬ወደ ሕዝቡም ሲደርሱ አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀረበና ተንበርክኮ። ጌታ ሆይ፥ ልጄን ማርልኝ፥ በጨረቃ እየተነሣበት ክፉኛ ይሣቀያልና፤ ፲፭ብዙ ጊዜ በእሳት ብዙ ጊዜም በውኃ ይወድቃልና። ፲፮ወደ ደቀ መዛሙርትህም አመጣሁት ሊፈውሱትም አቃታቸው አለው። ፲፯ኢየሱስም መልሶ። የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደዚህ ወደ እኔ አምጡት አለ። ፲፰ኢየሱስም ገሠጸው ጋኔኑም ከእርሱ ወጣ፥ ብላቴናውም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰ። ፲፱ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀረቡና። እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምን ነው? አሉት። ፳ኢየሱስም። ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ። ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም። ፳፩ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም አላቸው። ፳፪በገሊላም ሲመላለሱ ኢየሱስ። የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፥ ይገድሉትማል፥ ፳፫በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው። እጅግም አዘኑ። ፳፬ወደ ቅፍርናሆምም በመጡ ጊዜ ግብር የሚቀበሉ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ቀረቡና። መምህራችሁ ሁለቱን ዲናር*ፍ1* አይገብርምን? አሉት። ፳፭አዎን ይገብራል አለ። ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ኢየሱስ አስቀድሞ። ስምዖን ሆይ፥ ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸውን ወይስ ከእንግዶች? አለው። ፳፮ጴጥሮስም። ከእንግዶች ባለው ጊዜ ኢየሱስ። እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው። ፳፯ነገር ግን እንዳናሰናክላቸው፥ ወደ ባሕር ሂድና መቃጥን ጣል፥ መጀመሪያም የሚወጣውን ዓሣ ውሰድና አፉን ስትከፍት እስታቴር*ፍ2* ታገኛለህ፤ ያን ወስደህ ስለ እኔና ስለ አንተ ስጣቸው አለው።