፩ኢየሱስም አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማዘዝ በፈጸመ ጊዜ በከተሞቻቸው ሊያስተምርና ሊሰብክ ከዚያ አለፈ። ፪ዮሐንስም በወህኒ ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና። ፫የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ? አለው። ፬ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ፭ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ ፮ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው። ፯እነዚያም ሲሄዱ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ እንዲህም አለ። ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ፰ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን? እነሆ፥ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታት ቤት አሉ። ፱ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን። ፲እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ ፲፩ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነውና። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። ፲፪ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል። ፲፫ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፤ ፲፬ልትቀበሉትስ ብትወዱ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው። ፲፭የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። ፲፮ነገር ግን ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ። ፲፯እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም ይሉአቸዋል። ፲፰ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፥ እነርሱም። ጋኔን አለበት አሉት። ፲፱የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እነርሱም። እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል። ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች። ፳በዚያን ጊዜ የሚበዙ ተአምራት የተደረገባቸውን ከተማዎች ንስሐ ስላልገቡ ሊነቅፋቸው ጀመረ እንዲህም አለ። ፳፩ወዮልሽ ኮራዚ፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና። ፳፪ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። ፳፫አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበርና። ፳፬ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል። ፳፭በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ። አባት ሆይ፥ የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ ፳፮አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። ፳፯ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም። ፳፰እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ፳፱ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ፴ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።