፩ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም ቀርበው ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ለመኑት። ፪እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው። በመሸ ጊዜ። ሰማዩ ቀልቶአልና ብራ ይሆናል ትላላችሁ፤ ፫ማለዳም። ሰማዩ ደምኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል ትላላችሁ። የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ፥ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን? ፬ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ትቶአቸውም ሄደ። ፭ደቀ መዛሙርቱም ወደ ማዶ በመጡ ጊዜ እንጀራ መያዝን ረሱ። ፮ኢየሱስም። ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ አላቸው። ፯እነርሱም። እንጀራ ባንይዝ ነው ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ። ፰ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው። እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እንጀራ ስለ ሌላችሁ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና አታስተውሉምን? ፱ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፥ ስንት መሶብም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ፲ወይስ ለአራቱ ሺህ ሰባቱ እንጀራ፥ ስንት ቅርጫትም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን? ፲፩ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉምን? ፲፪እነርሱም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ያን ጊዜ አስተዋሉ። ፲፫ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን። ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ። ፲፬እነርሱም። አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። ፲፭እርሱም። እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ፲፮ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ። አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። ፲፯ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። ፲፰እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። ፲፱የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል። ፳ያን ጊዜም እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለማንም እንዳይነግሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ፳፩ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር። ፳፪ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ። አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ። ፳፫እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን። ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው። ፳፬በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ። እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ፳፭ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል። ፳፮ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? ፳፯የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል። ፳፰እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።