ኢየሱስም እነዚህን ቃሎች ሁሉ በፈጸመ ጊዜ፥ ለደቀ መዛሙርቱ። ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንዲሆን ታውቃላችሁ፥ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል አለ። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፥ ኢየሱስንም በተንኰል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ፤ ነገር ግን። በሕዝቡ ዘንድ ሁከት እንዳይነሣ በበዓል አይሁን አሉ። ኢየሱስም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የበዛ ሽቱ የሞላው የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች በማዕድም ተቀምጦ ሳለ በራሱ ላይ አፈሰሰችው። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቈጡና። ይህ ጥፋት ለምንድር ነው? ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና አሉ። ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው። መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና ሴቲቱንስ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? ፲፩ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ ፲፪እርስዋ ይህን ሽቱ በሰውነቴ ላይ አፍስሳ ለመቃብሬ አደረገች። ፲፫እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል። ፲፬በዚያን ጊዜ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ። ፲፭ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ? እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት። ፲፮ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር። ፲፯በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው። ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ አሉት። ፲፰እርሱም። ወደ ከተማ ከእገሌ ዘንድ ሄዳችሁ። መምህር። ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል በሉት አለ። ፲፱ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ ፋሲካንም አሰናዱ። በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ፳፩ሲበሉም። እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ። ፳፪እጅግም አዝነው እያንዳንዱ። ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር። ፳፫እርሱም መልሶ። ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፥ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው። ፳፬የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፥ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አለ። ፳፭አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ። መምህር ሆይ፥ እኔ እሆንን? አለ፤ አንተ አልህ አለው። ፳፮ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና። እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ፳፯ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ። ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ፳፰ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። ፳፱ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም። መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ። ፴፩በዚያን ጊዜ ኢየሱስ። በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና፤ ፴፪ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው። ፴፫ጴጥሮስም መልሶ። ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም አለው። ፴፬ኢየሱስ። እውነት እልሃለሁ፥ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። ፴፭ጴጥሮስ። ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም አለው። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ፴፮በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደምትባል ስፍራ መጣ ደቀ መዛሙርቱንም። ወዲያ ሄጄ ስጸልይ ሳለ በዚህ ተቀመጡ አላቸው። ፴፯ጴጥሮስንም ሁለቱንም የዘብዴዎስን ልጆች ወስዶ ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር። ፴፰ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ አላቸው። ፴፱ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ። አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ። ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጣ፤ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን። እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን? ፵፩ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው። ፵፪ደግሞ ሁለተኛ ሄዶ ጸለየና። አባቴ፥ ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁን አለ። ፵፫ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው። ፵፬ደግሞም ትቶአቸው ሄደ፥ ሦስተኛም ያንኑ ቃል ደግሞ ጸለየ። ፵፭ከዚያ ወዲያ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ። እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ እነሆ፥ ሰዓቲቱ ቀርባለች የሰው ልጅም በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ፵፮ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው። ፵፯ይህንም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሎች ዘንድ መጡ። ፵፰አሳልፎ የሚሰጠውም። የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ፵፱ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና። መምህር ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ብሎ ሳመው። ኢየሱስም። ወዳጄ ሆይ፥ ለምን ነገር መጣህ? አለው። በዚያን ጊዜ ቀረቡ እጃቸውንም በኢየሱስ ላይ ጭነው ያዙት። ፶፩እነሆም፥ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው። ፶፪በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው። ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ። ፶፫ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን? ፶፬እንዲህ ከሆነስ። እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ? ፶፭በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ለሕዝቡ። ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ ወጣችሁን? በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስቀመጥ ሳለሁ አልያዛችሁኝም። ፶፮ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነ የነቢያት መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ነው አለ። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ። ፶፯ኢየሱስን የያዙትም ጻፎችና ሽማግሎች ወደ ተከማቹበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ፶፰ጴጥሮስ ግን እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፥ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ። ፶፱የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ሸንጐውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙም፤ ብዙም የሐሰት ምስክሮች ምንም ቢቀርቡ አላገኙም። ፷፩በኋላም ሁለት ቀርበው። ይህ ሰው። የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ ብሎአል አሉ። ፷፪ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ። እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን? አለው። ፷፫ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም። አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ አለው። ፷፬ኢየሱስም። አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው። ፷፭በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ። ተሳድቦአል እንግዲህ ወዲህ ምስክሮች ስለ ምን ያስፈልገናል? እነሆ፥ ስድቡን አሁን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። ፷፮እነርሱም። ሞት ይገባዋል ብለው መለሱ። ፷፯በዚያን ጊዜ በፊቱ ተፉበት፤ ጐሰሙትም፥ ሌሎችም በጥፊ መትተው። ክርስቶስ ሆይ፥ በጥፊ የመታህ ማን ነው? ፷፰ትንቢት ተናገርልን አሉ። ፷፱ጴጥሮስም ከቤት ውጭ በአጥሩ ግቢ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድም ወደ እርሱ ቀርባ። አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው። እርሱ ግን። የምትዪውን አላውቀውም ብሎ በሁሉ ፊት ካደ። ፸፩ወደ በሩም ሲወጣ ሌላይቱ አየችውና በዚያ ላሉት። ይህ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ አለች። ፸፪ዳግመኛም ሲምል። ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ካደ። ፸፫ጥቂትም ቈይተው በዚያ ቆመው የነበሩ ቀርበው ጴጥሮስን። አነጋገርህ ይገልጥሃልና በእውነት አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ አሉት። ፸፬በዚያን ጊዜ። ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ሊራገምና ሊምል ጀመረ። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ። ፸፭ጴጥሮስም። ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።